Take a fresh look at your lifestyle.

ጀዋር መሐመድ ከ”ቲም ለማ” ጋር ምስጢራዊ ግንኙነት ነበረው?

(ቢቢሲ አማርኛ)

ጀዋር መሃመድ ከአገር ከወጣ 15 ዓመታትን አስቆጥሯል። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያን መሬት ከረገጠ አስር ዓመታትን ደፍኗል።

ገጠር አካባቢ ተወልዶ እንዳደገ የሚናገረው ጀዋር ለአዲስ አበባ ብዙም ትውስታ ባይኖረውም ያደገበት ገጠር ወንዙን ተራራውን ከህሊናው አልጠፉም። ልጅ ሳለ ባደገበት ቀዬ በኦነግና በኢህአዴግ መካካል ግጭት የነበረበት በመሆኑ “የልጅነት ትውስታዬ ከሌሎች ልጆች የተለየ ነው” ይላል። ትግል ውስጥ የገባውም ይህንን ሁነት ለመቀየር እንደሆነ ይናገራል። “ልጆቼ እኔ ባደኩበት ሁኔታ እንዲያድጉ አልሻም”

በእርሱ ላይና በሚመራው ሚዲያ ላይ ተመሥርቶ የነበረው የሸብርተኝነት ውንጀላ ከተነሳ ጀምሮ የጃዋር ወደ አገር ቤት ማቅናት ሲጠበቅ ነበር። ያ ቀን ነገ ቅዳሜ ሆኗል።

ጉዞውን አስመልክቶ ብዙዎች ስለ ደኅንነቱ ስጋት ገብቷቸው “የአትመለስ” ማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ጭምር ከፍተው ነበር። ይህ የወዳጆቹ ሥጋት የኢንጂነር ስመኘውን ግድያ ተከትሎ እየተጋጋመ መጥቶ ነበር።

“የእኔም ውሳኔ፣ የእነርሱም ስጋት ልክ ነው” የሚለው ጃዋር መንግሥት ለደኅንነቱ ዋስትናና ጥበቃ እንደሚያደርግለት አልሸሸገም።

የእርሱን ወደ አገር ቤት የመመለስ ፋይዳ ሲያጠናክርም “በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ በመቃወም ኢትዮጵያ አሁንም ብጥብጥ ውስጥ እንዳለች በማሳየት በአመራርና በሕዝቡ ላይ ያለውን በራስ መተማመን ለመሸርሸር ጥረት የሚያደርጉ ቡድኖች እንዳሉ ይናገራል።

ስለሆነም ይህንን አስተሳሰብ ለማዳከም የእርሱ ወደ አገር ቤት መመለስ አዎንታዊ ድርሻ እንደሚኖረው በጽኑ ያምናል።

በሕይወቱ ላይ የሚደርስ አደጋ ካለ እስከዛሬ የለፋበት በጎ ዓላማ ማራመጃ በመሆኑ እንደኪሳራ እንደማያየው ያስረዳል።

“ሕይወታችን በፈጣሪ እጅ እንጂ በፖሊስ እጅ ስላልሆነ፤ አደጋ ይመጣል ብለን ትግል አናቆምም” የሚለው ጀዋር ባለፉት አራት ዓመታት በእርሱ ላይ ሙከራዎች ተደርገው እንደነበርና የሥራ ባልደረቦቹ እንደተሰው አስታውሶ የርሱ ነፍስ ከሌሎች የተለየች እንዳልሆነች ይጠቅሳል።

ሐምሌ 30 ለጀዋር

የዛሬ ሁለት ዓመት ሐምሌ 30 በኦሮሚያ የተጠራው የተቃውሞ ሰልፍ አቶ ለማ መገርሳ ሥልጣን እንዲይዙ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበረው ይላል። ይቺን ቀን ታሪካዊ እንደሆነች በመጥቀስ።

በእንቅስቃሴውም ከሁለት መቶ በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡበት ይናገራል።

ባለፉት አራት ዓመታት 5 ሺህ ሰው እንደተሰዋ ገልፆ ለሚመጣው ለውጥ ክብሩን እንደሚያገኝ ሁሉ ለጠፋውም ኃላፊነቱን እወስዳለሁ ብሏል። ወደ ኢትዮጵያ የሚመለስበት ቀን ሃምሌ 30 መሆኑም ለዚሁ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ የተታቀደ ነው።

በዚሁም ዕለት የትግሉ እምብርት ሆና ወደምትወሰደው አምቦ፣ እንዲሁም ጊንጪና ጉደር አካባቢ በመሄድ በትግሉ ሕይወታቸውን ያጡ ግለሰብ ቤተሰቦችን የማግኘትና የማወያየት ፕሮግራም፤ እንዲሁም በእስርቤት የተጎዱትን የማቋቋምና የመርዳት ሥራ ለመሥራት እቅድ ይዟል።

ጀዋር ትግራይን ያውቃታል?

ከአገር ከመውጣቱ በፊት በአንድ ወቅት ለአፍታ አክሱም ይሂድ እንጂ የትግራእ ክልሉን በውል እንደማያውቀው ይናገራል።

ላለፉት 27 ዓመታት ህውሃት በሠራው ስህተት በትግራይና በሌሎች ክልሎች መራራቅ ተፈጥሯል ብሎ የሚያምነው ጀዋር ጉዞው ህውሃት የበላይነቱን በማጣቱ በኢህአዴግም ሆነ በክልሉ የተፈጠረውን ውጥረት የማርገብ ዓላማ እንዳለው አስታውቋል።

ከህውሃት አመራሮች፣ ከክልሉ ምሁራንና አዛውንቶች ጋር በመወያየት የመፍትሄ ሃሳብ ለማቅረብ እንደሚፈልግም ጨምሮ ተናግሯል ።

“ልባቸውን ከፍተው ካናገሩኝና ጆሯቸውን ሰጥተው ካዳመጡኝ፤ ጉዞዬ ከፍተኛ ስኬት እንደሆነ እቆጥረዋለሁ” ብሏል። ቁጭ ብሎ ከመነጋጋር በተለየ የማዳመጥ ሥራ መሥራት እፈልጋለሁ ሚለው ጅዋር “ሃሳባቸው ምንድን ነው” የሚለው ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ጠቅሷል። “በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች የመስጋትና የመከፋት ስሜቶችን ስለማይ ስጋታቸው ምን እንደሆነ በማዳመጥ የመፍትሔ ሃሳብ ለማቅረብ እሞክራለሁ” ብሏል

ጉዞው በዚህ ብቻ የሚጠናቀቅ ሳይሆን ከአማራ ህዝብ ጋር የተጀመረው የእርቅ ብቻ ሳይሆን የትግል አጋርነት ለማጠናከር ከክልሉ አመራርና ምሁራን ጋርም ውይይት ያደርጋል።

በምሥራቅ ኢትዮጵያ በሚኖረው ጉዞም በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት ለመፍታት ከአገር ሽማግሌዎችና ምሁራን ጋር ውይይት እንደሚያደርግም ገልጿል።

ጃዋር ራሱን እንደ ነጻ አውጪ ይመለከታል?

ሰላማዊ ትግልን በሚመለከት በተለያዩ በውጭ አገር በሚገኙ የትምህርት ተቋማት ለትግሉ የሚረዳውን እውቀት እንደቀሰመ ይናገራል።

ወጣቶችንም በዚህ ጉዳይ ላይ በማሰልጠን ትግሉ ላይ እንዲሰማሩ አብቅቷል።

ይሁን እንጂ ራሱን አንደለውጡ ቁልፍ ሳይሆን ሌት ተቀን በመሥራት ኃላፊነቱን እንደተወጣ አንድ ተራ ወጣት እንደሚቆጥር ይናገራል።

“ለውጡን ያመጡት የታገሉት ወጣቶች ናቸው” ይላል። ይህን የሚለው “ለፖለቲካዊ ትክክልነት” ፍጆታ ይሆን ወይስ በእርግጥም የሚያምንበት ሐሳብ ስለመሆኑ በቢቢሲ የተጠየቀው ጃዋር ይህንኑ ደጋግሞ አረጋግጧል። የነ ለማ ወደፊት መምጣትና ከነ ገዱ ጋር በመቆራኘት የሠሩት ሥራ አገሪቷን እንዳዳነም ጨምሮ አብራርቷል።

ከ “ቲም ለማ” ጋር ምስጢራዊ ግንኙነት?

አሁን ካሉት አመራሮች ጋር በትግሉ ወቅት የቀደመ ትውውቅ ስለመኖሩ የተጠየቀው ጀዋር ቀጥተኛ ምላሽ ለመስጠት ባይፈቅድም አሁን ያለው አመራር ወደፊት ገፍቶ እንዲመጣ ውስት ውስጡን ላለፉት አስርት ዓመታት በደህንነትም በወታደራዊ ክንፍ በርካታ ሥራ ሲሠራ መቆየቱን ለቢቢሲ ተናግሯል።

ነገር ግን ከእነርሱ ጋር ከመነጋገርና ከግንኙነቱ ይልቅ መናበቡ ያይል እንደነበር ያስታውሳል።

አሁን ወደፊት ከመጣው አመራር በተለይም ከ”ቲም ለማ” ጋር እነማን ተሳትፎ እንደነበራቸው ጀዋር በስም መጥቀስ ባይፈቅድም ወደፊት ታሪክ የሚያወጣው ነገር ይኖራል ሲል ጥያቄውን በደምሳሳው አልፎታል።

የጀዋር ገቢ ምንጭ ምንድን ነው?

የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር ኃ/ማሪያም ደሳለኝን የአንድ ወቅት ንግግር ጠቅሶ ” መቼም በጆንያ የሚሰጠኝ የለም” ሲል ከቀለደ በኋላ ዲያስፖራው የኦሮሞ ማህበረሰብ የሚያደርገውን ድጋፍ በስተቀር ከሌላ መንግሥትም ሆነ ቱጃር ግለሰብ የተገኘ ምንም ዓይነት ድጋፍ እንደሌለ ተናግሯል። ከመንግሥታት ጭምር ችሮታዎች የቀርቡ እንደነበር ነገር ግን ለመቀበል ፍቃደና ሳይሆኑ መቆየታቸውን ያስታውሳል።

በአጭር ጊዜ ውስጥ በአማርኛ ፣ በኦሮምኛ፣ በእንግሊዝኛና በሌሎች ቋንቋዎች ዕለታዊ ጋዜጣ እንዲሁም የራዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያ ለመክፈት በመጨረሻው ምዕራፍ እንደሚገኝም ተናግሯል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.