Take a fresh look at your lifestyle.

የኦቦ በቀለ ገርባ ነገር!

(የትነበርክ ታደለ)

በትናንትናው እለት 9ኛ ጉባኤውን ማካሄድ የጀመረው የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ባልተለመደ መልኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሮሞ ህዝብ ስም የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን ጋብዞ ነበር። በዚህ የመክፈቻ ስነ-ስርአት ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት መሪዎቹ በርካታ ክልላዊና ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውን የፖለቲካ ትንታኔ በማቅረብ የድርጅቱም ጉባኤ የተሳካ እንዲሆን በመመኘት ግብዣውን በአክብሮት ተቀብለው መገኘታቸውን ገልጸዋል።

የኦሮሞ ፌደራሊስት ፓርቲን ወክለው የተገኙት አቶ በቀለ ገርባም እንዲሁ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ትናንት በወቅቱ ንግግራቸውን ሳደምጠው እጅግ ስሜታዊ የሆኑና ከተገኙበት መድረክ ደርዝ የወጣ መሆኑን ታዝቤ “ምን ነካቸው?” እያልኩ ስብሰለሰል ነበር የዋልኩት።

ዛሬ ማለዳ ላይ ደግሞ ይህንኑ የአቶ በቀለ ገርባን ድርጊት አቶ ታዬ ደንደአ ክፉኛ ኮንነውት በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ ጽፈው አነበብኩ። ይሁን እንጂ የአቶ ታዬ ጽሁፍ አፍታም ሳይቆይ እንዲወርድ ተደርጓል።

አቶ በቀለ ገርባ ገና ንግግራቸውን ሲጀምሩ እንዲህ አሉ።……

“ይሄ ጉባኤ የተደረገው ባለፈው ሳምንት ቢሆን ኖሮ እዚህ መድረክ ላይ ፈጽሞ አልገኝም ነበር….” አሉና በሞቀ ጭብጨባ የተቀበላቸውን ህዝብ ኩም አደረጉት።

አቶ በቀለ አሁንም ፊታቸውን እንደቋጠሩ እልህና ንዴት በተምላው ስሜት ንግግራቸውን ቀጠሉ….

“…ባለፈው ሳምንት አንድ የ6 አመት ህጻን ተገድሏል….. ይህ ህጻን የተገደለው በሌላ ምክኒያት አይደለም:…….. ገዳዮቹ ኦሮሞ ስለሆነ ብቻ ነው ሮጦ ያልጠገበ ህጻን አሳደው የገደሉት።…… ይህን ጉዳይ እዚህ መጥቼ ለመናገር ነው ዛሬ የተገኘሁት……” በማለት የኦፒዲኦን ግብዣ አጣጥለው ተናገሩ።

ጥሩ ነው! የትኛውም ፖለቲከኛ የዜጎቹ ሞት፣ እስርና ስደት ከማንም በላይ እንዲህ ሊያመውና ሊያንገበግበው ይገባል። ነገር ግን አቶ በቀለ ገርባ በዚያ ታላቅ ጉባኤ ላይ ሲገኙ ሀሳባቸውን እንዲያንጸባርቁ አክብሮ የጋበዛቸውን ድርጂት፣ አባላቱንና መሪዎቹን ማክበር ይጠበቅባቸው ነበር።…… አቶ በቀለ ገርባ ከፊት ለፊታቸው የተቀመጡትን የሀገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትርና የክልሉን ፕሬዚዳንት በማክበር ንግግር ማድረግ ይጠበቅባቸው ነበር። …ይህ ህግ ባይሆንም ሀገራዊም አለማቀፋዊም ስርአት ነው።…..

ታዬ ደንደአ በኋላ ላይ ያጠፉት ጽውሁፋቸውም ይህንኑ የሚተች ነው! መከባበር ከቤት ይጀምራል። ዛሬ ኦሮሞ ነው የሚመራት የምትባለውን ኢትዮጵያ እያስተዳደሩ ያሉ፣ ይህን ጥቁር ጨለማ ወቅት የአንድነት መብራት እያበሩ ህዝቡን በጋራ ለማስተባበር ጥረት እያደረጉ ያሉ እነዚያ ሁለት ታላላቅ ሰዎች በእውነት ክብር ይገባቸው ነበር።….ድጋፍም አለሁ በይነትም ያስፈልጋቸው ነበር……. አቶ በቀለ ገርባ ግን ይህን ታላቅ ተግባር በስሜት ዘለሉት።

ይሄ ብቻ አይደለም!

የዚያን የስድስት አመት ህጻን ታሪክ ደጋግመው በመናገር ኦሮሞ በአንድ በሚታወቅ ቡድን ጥቃት እየደረሰበት እንደሆነ በመተንተን “አሁን ከማንኛውም ጊዜ በላይ አንድ ሆነን ይህን ጥቃት መመከት አለብን” የሚል ጠባጫሪ ንግግር ተናገሩ!…..

እኔ በግሌ ደንግጫለሁ! ደግነቱ ያን ህዝብ አውቀዋለሁ! እንዲህ ያለ ስሜታዊ የፖለቲካ ቅስቀሳን አላማውና ግቡ ምን እንደሆነ አሳምሮ የሚያውቅ ህዝብ ነው! ፖለቲካ ለዚያ ህዝብ ደግሞ አዲስ አይደለም! እናም የንግግራቸው ፍሬ ሀሳብ መልሶ ራሳቸውን አቶ በቀለ ገርባን አስመዘነበት እንጂ የትም አልሄደላቸውም!

Leave A Reply

Your email address will not be published.