Take a fresh look at your lifestyle.

የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት አመሰራረት ታሪክ ምን ይመስል ነበር?

በኢትዮጵያ ወጣቶች የስልጣኔ ትምህርት ቤት ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑን የተረዱት ግርማዊ ንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ ኃይለስላሴ (በዚያን ጊዜ የኢትዮጵያ መንግስት አልጋ ውራሽና እንደራሴ ልዑል ተፈሪ መኮንን ሲባሉ ሳሉ) አንድ ተማሪ ቤት በ፲፱፻፲፭ (1915) ዓም በዘመናዊ አሰራር አሰናዱ። ትምህርት ቤቱም “ተፈሪ መኮንን ተማሪ ቤት” ተብሎ በስማቸው ተጠራ።

ስለአዳሪዎች ተማሪዎች ለመኝታ የሚሆን ባለ ሶስት ፎቅ አንድ ትልቅ ቤት በ፲፱፻፲፮ (1916) ዓም ተሰራ። በዚህ አመት ዳግመኛ ለተማሪ ቤቱ ግቢ 25 ሄክታር መሬት ተከልሎ ዙሪያው አጥሩ በደንጊያ ካብ ታጠረ። በዚያ ዘመን ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን አውሮጳን ለማየት ሄደው ነበርና እዚያው ሳሉ የተማሪ ቤቱ ስራ በፍጥነት እንዲፈፀም ትእዛዝ አስተላልፈው ስለነበረ ደጅ አጋፋሪው ፊታውራሪ ገብረ ማርያምና የስራው ሹም ግራዝማች ወልደ ዮሐንስ ወልደ አብ በብርቱ ትጋት አሰርተው ስራው እንዲፈፀም አደረጉ። ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ከአውሮፓ ተመልሰው አዲስ አበባ በገቡ ጊዜ ስራውን ጎብኝተው ከፍፃሜው ደርሶ ስላሳያቸው እግዚአብሔርን አመሰገኑ።

ለትምህርት ስራ የሚያስፈልጉት መፃህፍትና ልዩ ልዩ ዓይነት መሳሪያዎች ከአውሮፓ እንዲመጡ ትእዛዝ ተደርጎ ነበርና እቃዎቹ በጥር ወር ፲፱፻፲፯ (1917 ) ዓም አ ዲስ አበባ ደረሰ። ከዚህም በኋላ ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን የተማሪ ቤቱን ደንብ በ፶፫ (53) አንቀፅ አዘጋጅተው ስለሠጡ በብርሃንና ሰላም ጋዤጣ ታትሞ ህዝብ እንዲያውቀው አደረጉ። ሚያዚያ 19 1917 ዓም ክቡራን ሚኒስትሮች፣ መኳንንትና ወይዛዝር፤ ኮር ዲፕሎሎማቲክና ታላላቅ የውጭ አገር ሰዎች ሁሉ በተገኙበት ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ተማሪ ቤቱን መርቀው ከፈቱ።

በዚያ በመጀመሪያው ጊዜያት የአዳሪዎች ተማሪዎች ቁጥር 30 ሲሆን፣ የተመላላሾች ቁጥር 50 አይበልጥም ነበር። የነበሩት መምህራንና ሹማምንት ደግሞ የሚከተሉት ነበሩ።

1.ክቡር ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ፣ ዋና ሹም

2.አቶ መርስኤ ኀዘን ወልድ ቂርቆስ፣ የግዕዝና የአማርኛ አስተማሪ

3.ሙሴ ጃን ጎዮን፣ ዳይሬክቴር፣ የፈረንሳይኛ አስተማሪ

4.አቶ ተዐውቀ ሀብተ ወልድ ፣ የፈረንሳይኛ አስተማሪ

5.ሙሴ ፖል፣ ላቡርዳሪ፣ የፈረንሳይኛ አስተማሪ

6.ሙሴ ናልባነዲያን፣ የሚዚቃ አስተማሪ

7.አቶ ኤፍሬም ተወልደ መድኅን፣ የእንግሊዠኛ አስተማሪ

8.ሙሴ ፓፓዚያን፣ የስዕል አስተማሪ

9.አቶ መንገሻ ከፈላ

10.አቶ ደምሴ ወልደየስ፣ ዋና ፀሃፊ

በዚሁ የመጀመሪያ አመት የተማሪዎች ምግብ ከልዑል አልጋ ወራሽ ግቢ በተለይ እየተሰናዳ ይመጣ ነበርና የተማሪዎች ምቾት ከመጠን ያለፈ ነበር። ተማሪ ቤቱ በዚያ በመጀመሪያው ሰዓት እንኳን በተለየ የራሱ መዝሙር ነበረው። ከዚያ በፊት በአማርኛ የተፃፈ መዝሙር መዘመር አልተጀመረም ነበርና የተፈሪ መኮንን ተማሪ ቤት መዝሙር በተዘመረ ጊዜ እንደ ብርቅ ሆኖ ታየ። መዝሙሩ የተደረሰው ወዲያው ትምህርት ቤቱ እንደተከፈተ በእንግሊዝኛ አስተማሪው አቶ እፍሬም ተወልደ መድህን ነበር። መዝሙሩም የሚከተለው ነበር።

 

የኢትዮጵያን ብርሃን፤

ዘለዓለም ያኑርልን፤

የነፃነት አምባችንን፤

አምላክ ይጠብቅልን።

ለሦስቱ ቀለሞች ጽናት፤

ላገር ለህዝባችን ልማት፤

እውቀት እውነት ሊነግሱብን።

ተፈሪን ያኑርልን።

የተ.መ.ተ.ቤ. ተማሪዎች፤

ለነፃነት ብሎ መሞት፤

ይህ ነው የኛ ዋናው የኛ ምኞት፤

ለሦስቱ ቀለሞች ፅናት

ላገር ለህዝባችን ልማት።

እውቀት እውነት ሊነግሱብን፣

ተፈሪን ያኑርልን።

ተፈሪ መኮንን ባፀደቁት የተማሪ ቤቱ ደንብ አስተማሪዎች የሚያርፉበት የበአል ቀን እንደሚከተለው ነበር።

1.እሁድ በየሳምንቱ

2.መስከረም ፩ ቀን አዲስ አመት

3.መስከረም ፲፮ ቀን በዓለ መስቀል

4.ታህሳሥ ፳፱ ቀን በሃለ ልደት

5.ጥር ፲፩ ቀን፣ በዓለ ጥምቀት

6.ጥር ፳፩ ቀን፣ አስተርእዮ በዓለ ማርያም

7.የካቲት ፳፫ ቀን፣ የመንግስት በዓል

8.በዓለ ስቅለት

9.ቅዳሜ ሥዑር (ከስቅለት በኋላ ያለው ቅዳሜ)

10.በዓለ ትንሳኤና ስምንቱ ቀን በዓለ ፋሲካ

11.የአውሮጳ የልደት በዓል

12.የአውሮፓዎች ዘመን መለወጫ

13.የአውሮፓዎች ስቅለትና ፋሲካ

ደግሞ ከሐምሌ ፩ ቀን እስከ መስከረም ፩ ቀን ሁለት ወር ሙሉ የትምህርት ቤቱ ይዘጋልና እረፍት ያደርጋሉ። ከዚህ በላይ ከተቆጠሩት ቀኖች በቀር አስተማሪዎች ሁሉ በተወሰነ ሰዓት ወደ ትምህርት ቤት እየገቡ ያስተምራሉ።

ምንጭ፡ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት አጭር ታሪክ (ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት)

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.