Take a fresh look at your lifestyle.

ከአንድ ከተማ ያነሰው የአማራ በጀት ጉዳይ!

(ጌታቸው ሺፈራው)

የዘንድሮ አማራ ክልል በጀት 43 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ተገልፆአል! ከአዲስ አበባ በአንድ ቢሊዮን ያንሳል። ቁም ነገሩ የአዲስ አበባ አንድ ቢሊዮን መብለጡ አይደለም። አዲስ አበባም በርካታ ድሃ ያለበት ከተማ ነው። በርካታ ችግሮች ያሉበት ከተማ ነው። ከአማራ ክልል ጋር ግን ሊነፃፃር አይችልም።

~ አማራ ክልል ውስጥ ያሉት ከግማሽ በላይ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የዳስ ናቸው። ዳስ ብርቅ የሆነባቸው አካባቢዎችም አሉ። ግንድ ላይ “1ኛ ክፍል” ተብሎ ተፅፎ “ትምህርት ቤት ነው” የተባለባቸው አካባቢዎች አሉ። እናቶች ወደ ህክምና ተቋም የሚሄዱት በቃሬዛ ነው። ወንዝ የሚሻገሩት በገመድ ነው! ይህ ጉድ በፎቶ ሲወጣ አስደንጋጭ ነበር። ነገር ግን ከዚህ የባሰ ድህነትም አለ።

~አማራ ክልል ውስጥ 190 በላይ ፕሮጀክቶች መክነዋል። ትንንሾቹን ከተሞች ትተን ደብረ ብርሃን፣ ጎንደር፣ ደሴና ባህርዳር መሰረተ ልማታቸው የሚያሳዝን ነው። ከአራቱ ከተሞች መካከል ውሃና መብራት በሳምንት አንድ ጊዜ የማያገኙ ከተሞች አሉ። ቀሪዎቹማ ሳምንታትና ወርም አገልግሎት ያጣሉ። ጎንደርና ደሴ ከነበራቸውም በእጅጉ ወደኋላ ተመልሰዋል። መንገዳቸው ተላልጦ ባዶ ሆኗል። ሆቴሎቻቸው ባዶ ናቸው። በዓለም የታወቁ የቱሪዝም መስዕቦች በአገልግሎት እጦት (መንገድ፣ መብራትና ውሃ) ምክንያት ጎብኝ የላቸውም። እድሳት አይደረግላቸውም፣ ሆን ብለው እንዲፈርሱ ለሬድዮ ጣቢያዎች ጨምሮ ለኪራይ እንዲሰጡ ሆኗል።

~የደሴ ሆስፒታል ብዙ ተወርቶለት በወሬ ቀርቷል፣ የክልሉ ዋና ከተማ ባህርዳር የሚገኘው ሆስፒታል ቀዶ ጥገና አገልግሎት የሚሰጠው በዣንጥላ ነው። በሀገሪቱ ቀዳሚው የጎንደር ሆስፒታል ህሙማን ለወራት የሚተኙት በረንዳ ላይ ነው።

~ፋብሪካዎች እንዳይነገቡ የውሃና መብራት አቅርቦት የለም። የኤሌክትሪክ ማከፋፈያዎቹ በደርግ ዘመን የተሰሩ ናቸው። ክልሉ ለትህነግ/ህወሓት ጥሬ እቃ አቅራቢ እንጅ አምራች እንዳይሆን ኢንዱስትሪዎችን እንዳይተከሉ ተደርገዋል። ባህርዳር ላይ የእንጨት፣ ደብረ ማርቆስ ላይ የመኪና መገጣጠሚያ እንዳይተከል መከልከሉ ይነገራል። የወልቃይት ተወላጆች ጎንደር ላይ መዋለ ንዋይ ከሚያፈሱ ትግራይ ላይ እንዲያደርጉት እንደሚነገራቸው አጫውተውኛል። የደሴ ከተማ ነጋዴዎች ሆን ተብሎ ከከተማው እንዲፈልሱ ተደርገዋል። (ዝርዝሩን ወደፊት የሚሰራ ይሆናል) ባህርዳር ጣናን ያህል ሀብት እንዳላት ከተማ አይደለችም።

~በኢትዮጵያ በድህነት የተደቆሰው ሕዝብ የሚገኘው አማራ ክልል ያለ ሕዝብ መሆኑ በዓለም አቀፍ ሪፖርትም ይፋ ሆኗል። በኢትዮጵያ አማካይ በከፋ ድህነት የሚኖረው ሕዝብ መጠን 23በመቶ፣ እንዲሁም በአማራ ክልል ሕዝብ መካከል 26 በመቶ መሆኑ በዓለም አቀፍ ሪፖርት ሰፍሯል። የአማራ ክልል በኢትዮጵያ በከፋ ድህነት ላይ የሚገኝ፣ ኢትዮጵያ እንደሀገር ከገጠማት የከፋ ድህነትም የባሰ ሆኖ ተመዝግቧል። በኢትዮጵያ “ቀንጭረው” የሚወለዱ ሕፃናት በመቶ 38 ሲሆኑ፣ በአማራ ክልል 46.3 ነው። በትምህርት ጥራት፣ በጤና ጥበቃ፣ በመሰረተ ልማት አማራ ክልል በኢትዮጵያ አንደኛ ነው። ዝቅተኛ ደረጃ በመሆን። በሀገር አቀፍ ደረጃ ካሉት ችግሮች 1ኛው አማራ ክልል ነው። በሀገር ደረጃ ካለው ዝቅተኛ ኢኮኖሚ መሰረት የአማራ ክልል ያነሰ ነው።

~ይህ ድህነት ከምንም የመጣ አይደለም። የበጀት ጉዳይ አንዱ ነው። ገዥዎችና አስገዥዎች ያደረጉት ነው። አደህይቶ መግዛት ነው። በአንድ ወቅት በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ጠፋ ተብሎ በፓርላማ ተነግሯል። አላማው ግልፅ ነው። በጀት መቀነሻም ጭምር ነው! ዛሬም ይህ በድህነት የደቆሱትን ክልል ከአንድ ከተማ ያነሰ በጀት ሰጥተውታል! ይህንም በዚህ በዛ ብለው ሲቦጭቁት ከግማሽ ያነሰው እንኳ ለሕዝብ አይደርስም።

~ይህ ሆኖ ደግሞ አማራ ክልል ከፍተኛ ግብር የተጣለበት ክልል ነው። በየ አመቱ ቢለያይም አማራ ክልል ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ (በአብዛኛው አንደኛ፣ ሁለተኛ ደረጃ) ከፋይ ነው። ለፌደራል መንግስቱ ግብር በመክፈል አንደኛ ወይንም ሁለተኛ ነው!

~ሁለት አይነት የግብር አከፋፈል ስርዓት አለ። አንዱ ለክልሉ ነው። ሁለተኛው በፌደራል ነው። በክልል ደረጃ የሚከፍሉት ከፒ ኤል ሲ በላይ ያሉት ናቸው። ከዛ በታች ያሉት ለክልሉ ነው ግብር የሚከፍሉት። ሆኖም ለክልሉ ግብር የሚከፍሉት ለፌደራል መንግስቱ እንዲከፍሉ ከፍተኛ ጫና፣ከፍተኛ ግብር ይጣልባቸዋል። ከዚህ ግብር ለመላቀቅ በፒ አል ሲ ስም ይቀይሩና ለፌደራል ይከፍላሉ። ለክልሉ መንግስት ግብር ሲከፍሉ የሚማሩባቸው በርካታ ነገሮች አሉ። በዚህ ምሬት ምክንያት አብዛኛዎቹ ለፌደራል መንግስቱ ለመክፈል ተገድደዋል። ለአብነት ያህል ጎንደር ከተማ ውስጥ ከሚገኙት ነጋዴዎች መካከል 43 በመቶዎቹ ብቻ ለክልሉ ይከፍላሉ። 57 በመቶ ለፌደራል እንዲከፍሉ ተገድደዋል። በከተማው በፌደራል ደረጃ የመክፈል አቅም ያላቸው (ከፍተኛ ግብር ከፋይ) የተወሰኑ ቢሆኑም፣ ለክልሉ ሲከፍሉ ከሚጫንባቸው የፌደራሉ ግብር ስለሚሸል አነስተኛ ንግድ ቤቶችም ለክልሉ መንግስት እንዳይከፍሉ ተገድደዋል።

ምክንያታዊ የግብር አከፋፈልም ሆነ፣ በጀት ምደባ ቢኖር ሊመረጥ የሚችልው የከፋ ድህነት ያለበት ክልል ነበር። በዚህ ደግሞ 1ኛው አማራ ክልል ነው። ቢያንስ ቢያንስ እንኳ ከአንድ ከተማ ያነሰ በጀት ሊበጀትለት አይችልም ነበር። በአንድ ወቅት በይፋ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝቡ ጠፋ ተብሏል። እነዛ ገዥዎች አሁን ፊት ላይ አይደሉም። ይሻላሉ በተባሉት የእነ አብይ ዘመንም የአማራ ክልል በጀት ከአንድ ከተማ ያነሰ ሆኗል!

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.