Take a fresh look at your lifestyle.

“ነፃ የወጡ የፌስቡክ ህዝቦችን እና የሰሞኑን ግርግር ተመልከቱ” በሶሊያና ሽመልስ

ሃሳብን በነፃነት ለመግለፅ መብት ኡኡ ስንል የነበርን እና በየደረጃው መስዋእትነት የከፈልን ሁሉ አሁን በአንፃራዊ ነፃነቱን የምንጠቀምበት መንገድ የሚያስተዛዝብ ብቻ ሳይሆን የሚያሳፍር ነው ፣ በአሳፋሪነቱ ተዛዝበን እንዳናልፈው ደሞ በተግባርም ንብረት ውድመት እና አካል ጉዳት የሚያመጣ አጋጋይ ፋክተር ሆኖ መገኘቱ ነው።

ይህንን መብት የሚጠቀሙ “ነፃ የወጡ የፌስቡክ ህዝቦችን” እና የሰሞኑን ግርግር ተመልከቱ ።

አንዱ ቡድን ሰገጤ፣ ከተማችን አትድረሱ ጀምሮ አዲስ አበባ የተለየች ማርስ ላይ ያለች ብርቅ ከተማ ሆና ሌሎችን የምትጠየፍ አድርጎ ሲሳደብ ሲንቅ ፣ እንጨት እንጨት በሚል ቀልድ ሲያንቋሽሽ ይውላል፣ ላይክ አለው ፣ ሼር አለው ፣ ሳቅ አለው ፣ ለነሱ ይሄ ጨዋታ ነው ።

ሌላው ደሞ ፈሪ ፣ የሚኒሊክ ሰፋሪ ፣ ከከተማችን እናስወጣለን፣ የኛ ነው ብሎ በአንድ አገር ውስጥ የሚኖሩ ከተለያዮ ብሄሮች እና በብሄር ማንነቶች የማይገለፁ ነዋሪዎች ያሉበትን ከተማ የአንድ ታሪካዊ ሂደት ቀጥተኛ ደም ወራሽ እና ርዝራዥ አድርጎ ፓለቲካ ፓርቲ በቅጡ ካደራጀው 14 አመት የሞላውን እና የፓለቲካ ንቃቱ በንፅፅር ያን ያህል ያልደረጀ ያልሆነውን ወጣት የፓለቲካ ጠላቱ ተወካይ አድርጎ ሲያቀርብ ኖሯል፣ ከርሟል

ይሄ ብሽሽቅ ከ”ፌስቡክ ኤሊትስ” ክርክር እና ጨዋታነት ዘሎ ንግግሩ በተግባር መሬት ላይ ያለውን ግንኙነት መልክ ላይ ተፅእኖ ሲያመጣ እንኳን ኸረ ይሄ ነገር እየከፋ ነው እስቲ ቀዝቀዝ እናድርገው ሃላፊነት በሚሰማን መልኩ እናውራ የሚል ብዙ ሰው አልተገኘም ።

ጭራሽ የእኔ ቡድን ይበልጥ ተጠቃ የእኔ ቡድን ተጠቃ ሆኖ ሁለቱም ጎራ ተጎጂ + ፎካሪ+ ተሳዳቢ ባህሪይ ይዘው የባንዲራ ፀቡን አጠናክረው ቀጥለዋል። እነዚህ መነሻ መሰረታዊ የትርክት ችግሮች የታወቁ የአገሪቱ fault lines ናቸው መፍትሄው ገና ሩቅ መንገድ የሚያስኬድ እልህ አስጨራሽ ነው። ነገር ግን የመፍትሄው አካል መሆን የሚፈልግ ማንኛውም ግለሰብ ከተንኳሽ ህዝብ ለህዝብ ከሚያቃቅር አጓጉል ብሽሽቅ በመራቅ መጀመር ነበረበት፣ ለዛ አልታደልንም።

ትላንትና ዛሬ አዲስ አበባ ላይ ሰው ሞቷል፣ ንብረት ጠፍቷል፣ በመንግስት እጅ ሳይሆን በማይረባ፣ ባልታሰበበት ፣ ለምንድነው ይህ የሆነው ተብለን ብንጠየቅ በግልፅ ለማስረዳት በማንችልበት ምክንያት ወጣቶቻችን ተጋጭተዋል።በብሽሽቁ እና ወጣቶቹን በማጦዙ አንድ ላይክ፣ አንድ ስታተስ ፣ አንድ ፉከራ፣ አንድ ኮመንት አስተዋእፃ ያደረገ ሁሉም ሰው በአንድ ሆነ በሌላ መልኩ ለዚህ ጥፋት እጁ አለበት።

አሁንም የፀብ ቡድኖችን የብሄር መልክ ሰጥታችሁ ፣ ነገሮችን ከፕሮፓርሽን አውጥታችሁ የምታግሉ ሰዎች እጃችሁ ጥፋቱ ውስጥ ጎልቶ እንደሚታይ አስቡት። በዚህ መሃል ደሞ ብዙ ያጠፋም ብዙ የጠፋበትም ሁለቱም አሸናፊ አይደለም።

አዲስ አበባ ለሺህ ባንዲራ ትበቃለች፣ አሳዛኙ ነገር የሞተውም ሆነ የተጎዳው ሰው የሚጋራው ለዚህ ነው እኮ የሞተው/ የተጎዳው የሚያስብል የጋራ ነገር ለመመስረት ተስፋችን ከመነሻው መጨለሙ ነው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.