Take a fresh look at your lifestyle.

በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

የተከበርኸው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም በአገር ውስጥም ሆነ በመላው ዓለም ያላችሁ የአማራ ተወላጆች ፤

የተከበራችሁ የንቅናቄያችን አባላትና ደጋፊዎች፤

የተከበራችሁ በአገር ቤትም ሆነ በውጭ የምትገኙ ልዩ ልዩ የአማራ ድርጅቶችና ማኅበራት፤

ክቡራንና ክቡራት፤

ከሁሉ አስቀድመን በአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ – አብን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስም እንኳን ለ2011 አዲስ ዓመት አደረሳችሁ ፣ አደረሰን ማለት እንፈልጋለን፡፡

እንደሚታወቀዉ ባለፉት 50 የሚጠጉ ዓመታት በአጠቃላይና በተለይም ባለፉት 27 የግፍ ዓመታት አማራው የሚወክለውና ጥብቅና የሚቆምለት ኃቀኛ የፖለቲካ ድርጅት ባለመኖሩ አማራውን እንደሕዝብ ጠላቴ ነው ብለው በተነሱ ብሔርተኛ ኃይሎች አማካኝነት በየትኛውም መስፈርት ቢለካ ተቀባይነት የሌለውና በሰው ልጆች ላይ ይደረጋል ብቻ ሳይሆን ለማድረግ ይታሰባል ተብሎ እንኳን ለመገመት አዳጋች በሆነ መልኩ ዘግናኝ የዘር ማጥፋት ፣ ዘር ማጥራትና ዘር ማሳሳት ወንጀሎች እየተፈፀሙብን ይገኛል፡፡ አማራ ጠል፣አግላይና ነጣይ ብሔርተኛ ኃይሎች አገራዊ የፖለቲካ ሥልጣን በመያዛቸው በትግል ወቅት በማንፌስቶ ጭምር ያንፀባርቁት የነበረውን የአማራ ጥላቻቸውን መንግሥታዊ ተቋማዊ ቅርፅ በመስጠት በፖሊሲ ደረጃ ጭምር አማራውን የማጥፋት ተልዕኮ ቀጥለውበታል፡፡ አማራው ላይ የሚደርሰው እልቂት፣ግፍና መከራ ሊቆም ይገባል ሲሉ የሞገቱ ታዋቂ ግለሰቦችና አደረጃጀቶችም በሥርዓቱ አፈና መዋቅር ተጠልፈው ወድቀዋል፡፡ በዚህ ረገድ ታላቁ የአማራ ሰማዕት ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ግንባር ቀደም የጨቋኝ ሥርዓቱ ገፈታ ቀማሽ ናቸው፡፡

የትግራይ ሕዝብ ነፃነት ግምባር-ትህነግና የኦሮሞ ነፃነት ግምባር-ኦነግ በሰሩት የፖለቲካ ድራማ በበደኖ ፣ በአርባጉጉ ፣ በሐረር ፣ በእንቁፍቱ ፣ በወተር ፣ በአሰቦት ገዳም፣ ወዘተ. በአማራው ላይ የደረሰው የዘር ፍጅት ቁስል በአግባቡ ሳይጠግ እና ጥፋተኞች ለፍትኅ ሳይቀርቡ ፤ ይህንን የተቃወሙ የአማራ አሳቢዎችና ታላላቅ ሰዎች ከሚሰሩባቸው ተቋማት በግፍ መባረርን ጨምሮ በርካቶች ከእስር አስከ ከአገር መሳደድና ሞት ድረስ የዘለቀ መከራን ተቀብለዋል፡፡ በዚህ የተነሳም አማራውን ተቋማዊ በሆነ መንገድ ሁለንተናዊ

የመነጠል፣ማግለል፣ማፈናቀልና ማሳደድ ግፎች ያለሀይ ባይ በትህነግ መራሹ ሥርዓት ላለፉት 27 ዓመታት በላይ ሲፈፀሙ ኑረዋል፡፡

ትህነግና ሌሎች አማራ ጠል ግብረአብሮች አማራው ላይ በስልታዊና ተቋማዊ መንገድ ከመነጠልና ማግለል ባለፈ ለም መሬቶቹን በጉልበት ወደ ተለያዩ የአስተዳደር ክልሎች በማካለል የርስት ነጠቃና ባለርስት አማራዎች ላይም በግዳጅ ሌላ ማንነትን እንዲቀበሉ የማድረግ የማንነት ገፈፋ ወንጀል ሰርተዋል፡፡

በአማራው ላይ ከሚደርሰው የማንነት ገፈፋና ርስት ነጠቃ እንዲሁም ማፈናቀል፣ማሳደድ፣እስር፣እንግልትና ግድያ በተጨማሪ አማራው በመልማት ፀጋውና ለአገር ልማት ባበረከተው አስተዋፅዖ ልክ እንዲለማና ፍትኃዊ ተጠቃሚ እንዲሆን አልተደረገም፡፡ ይልቁንም ባለፉት 27 ዓመታት አማራው ሲበዘብዝና በመዋቅራዊ ሁኔታ የማደኽየት ወንጀል ሲሰራበት ነበር፡፡ የዓለም ባንክ የአማራ ክልል ተብሎ ታጥሮ የተቀመጠውን አማራውን የማሰቃያ ክልል በመንገድ ተደራሽነት ጭራ እና በመብራት ተደራሽነትም ጨለማው ሲል እ.ኤ.አ በ2017 ባወጣው ሪፖርቱ ይገልፀዋል፡፡ አማራ በጤና ተቋማት ተደራሽነትና የአገልግሎት ዝግጁነት እጅግ ዝቅተኛ በሚባል ደረጃ የሚገኝ ሲሆን ሞተው በሚወለዱና በጨቅላ ሕፃናት ሞት ፣ በሕፃናት መቀንጨር ፣ በወሊድ መቆጣጠሪያ አጠቃቀምና በወሊድ ምጣኔ እንደአገር የመጀመሪያውን ደረጃ ይይዛል፡፡ በት/ት ጥራትና ተደራሽነት በኩልም እጅግ አስከፊ በሚባል እና የመንደር ዛፎች ሳይቀር በት/ቤትነት የሚቆጠሩበት ክልል ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው እንደአገር 2/3ኛውን የምግብ እህል በሚያመርተው፤በቀንድ ከብትም 1/4ኛውን በያዘው ሕዝባችን ነው፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ እነዚህንና እነዚህን መሰል በአማራው ላይ የተደቀኑ የኅልውና ፈተናዎችን በመቀልበስ ሁላችንንም በእኩልነትና ፍትኃዊነት የምታስተናግድ ዴሞክራሲያዊትና ማኅበራዊ ፍትኅ የነገሰባት ኢትዮጵያን ከሌሎች ወንድም ሕዝቦችና የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በመሆን ለመገንባት ነው ሰኔ 3/2010 ዓ.ም የተመሰረተው፡፡ አብን ከተመሰረተ ዛሬ 112 ቀናት ሆነውታል፡፡ በእነዚህ ቀናት ውስጥ በ12 ትልልቅ ከተሞች አስከ 100 ሺህ የሚቆጠር ሕዝብ የተሳተፈባቸው መድረኮችን አዘጋጅቷል ፤ ዋና ጽ/ቤትን ጨምሮ ከ60 በላይ የዞንና የወረዳ ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶችን አደራጅቷል ፤ እንዲሁም ከ160 ሺህ በላይ አባላትንና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደጋፊዎችን አፍርቷል፡፡

አብን ከዚህ በታች የተዘረዘሩት 6 መሰረታዊ የአማራ ሕዝብ የኅልውና ጥያቄዎች ተገቢው ምላሽ እንዲያገኙ ይታገላል፡፡ እነሱም፡-

 1. የአማራን ሕዝባዊና ግዛታዊ አንድነትና ኢተነጣጣይነት መብት ማስከበር
 2. አማራ ለአገር ልማት ባበረከተው አስተዋጽዖና በመልማት ፀጋው ልክ የሚኖረውን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ
 3. በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚኖሩ አማራዎች ማንነታቸውን የማበልፀግ ፣ የፖለቲካ ውክልና የማግኘትና ራስን በራስ ማስተዳደር መብታቸውን ማስከበር
 4. አማራው በቁመቱና በወርዱ ልክ በአገር ሁለንተናዊ ተሳትፎ የሚኖረውን ድርሻ ማስከበር
 5. የአማራ ህዝብ ፍላጎት ያልተካተተበትና ያለአማራዉ ተሳትፎ የተዘጋጀዉ ፣ አማራዉን በጨቋኝነት የሚወነጅለዉ የኢፌዴሪ ህገ መንግስት እንዲሻሻል ወይም እንዲቀየር
 6. አማራው እስካሁን ለደረሰበት ግፍና ዘር ማጥፋት ይቅርታ እንዲጠየቅና ተመጣጣኝ የልማት ካሳ እንዲያገኝ ማድረግ ናቸው፡፡

ላለፉት 27 ዓመታት አማራው ለብቻው መከራውን ሲያይባቸው የነበሩ አግላይና ነጣይ መንግስታዊ ስሪቶችና ሥርዓቶች ውለው አድረው ወላፈናቸው ሌሎችንም ሕዝቦች በማዳረሳቸው በአገርአቀፍ ደረጃ ሕዝባዊ እምቢተኝነትን በመቀስቀስ በሥርዓቱ ዘንድ ጥገናዊ ለውጥን ያለውድ በግድ አስከትለዋል፡፡ ይህን ተከትሎም የነፃነት፣ፍትኅና እኩልነት ጥያቄ በማንሳታቸው ብቻ ለዘመናት በግፍ እስር ሲማቅቁ የነበሩ ዜጎች ለመፈታት በቅተዋል፡፡ በውጭ አገራት እንወክለዋለን ለሚሉት ማኅበረሰብና አስተሳሰብ ያዋጣናል ባሉት መስክ ሲታገሉ የነበሩ የፖለቲካ ኃይሎችም በምኅረትና ይቅርታ ወደ አገር ቤት እንዲገቡ ተደርገዋል፡፡ በ‹‹መደመርና ይቅርታ›› የጠቅላይ ሚ/ር አብይ አህመድ እሳቤ የዘር ማጥፋት ወንጀልን ጨምሮ በአገር ኅልውና ፣ ንብረትና ኃብት ላይ ከፍተኛ አዳጋ ያደረሱና ያቀነባበሩ ግለሰቦችና ቡድኖችም በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ሆነዋል፡፡ አብን እነዚህንና እነዚህን መሰል እርምጃዎችን በመርህ ደረጃ በአዎንታ ይመለከታቸዋል፡፡ ይሁንና አብን እውነተኛ አንድነት ፣ ዘላቂ ሰላምና አገራዊ መተማመን ይሰፍን ዘንድ ከሁሉም በፊት ጥፋተኞች ሊታወቁና ላጠፉት ጥፋትም ወይ ይቅርታ ሊጠይቁ አልያም ወደ ፍትኅ ሊቀርቡ ይገባል የሚል ፅኑ አቋም አለው፡፡ ከይቅርታ በፊት እውነትን ማወቅ ይቀድማል፡፡ ተበዳይ ፍትኅ ሳያገኝና በዳይም ይቅርታ ባልጠየቀበት ሁኔታ በደፈናው መደመርና ይቅርታ አንድም ፍትኅን ማድበስበስ፤ ሁለትም ለበዳይ መወገን ነው፡፡ ስለሆነም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በበዓለ ሲመታቸው ወቅት የተናገሩትን ለፍትኅ የመወገን ቃላቸውን እንዲያከብሩ አብን ጥሪውን ያቀርባል፡፡

በሌላ በኩል አሁን ያለው ለውጥ ጥገናዊ ቢሆንም ይህ የተስፋ ጭላንጭል እንዲታይ የአማራ ሕዝብ ከማንም ያልተናነሰ ትግል የታገለና መስዕዋትነትም የከፈለ ቢሆንም ዛሬም ድረስ የታገለላቸው የኅልውና ጥያቄዎች እንኳንስና ሊፈቱለት በአግባቡ እንኳን አልተደመጡለትም፡፡ ከህግ አግባብ ዉጭ ወደ ትግራይ ክልል የተካለሉ የወልቃይት ፣ ጠገዴና ራያ ህዝባችንና ርስተ-ምድራችን ዛሬም ድረስ የትህነግ እልቂት አታሞ የሚደለቅባቸው ሆነው ቀጥለዋል፡፡ የአማራ ማንነት ጥያቄያቸውን በሰላማዊ መንገድ ያቀረቡ ወገኖቻችን ላይ የሚደርሰው እስር፣እንግልት፣ማፈናቀልና ግድያ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ የጎጃም አማራ አብይ ርስት በነበረው መተከል የሚኖሩ አማራ ወገኖቻችን እጅግ ሰቅጣጭ በሆነ መልኩ ታርደው እየተገደሉ፤መራቢያ አካላቸው እየተቆረጠ እና ከርስታቸው ተፈናቅለው ሜዳ ላይ እንዲወድቁ ተደርጓል፡፡

በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ አማራዎች ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬና ይዞታቸው ‹‹መጤ›› ተብለው ተፈናቅለው ለከፍተኛ ሰብአዊ ችግር ተጋልጠው ይገኛሉ፡፡ አርሶአደር አማራዎችም የይዞታ መሬታቸው በኃይል ተነጥቆ ለወጣቶች ተከፋፍሎባቸዋል፡፡ በጅጅጋ በተካሄደው እልቂትም አማራዎች

የአካልና ሕይወት መጉደልና መጥፋትን ጨምሮ ለከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ ተዳርገዋል፡፡ ከሰሞኑም በተደራጁ ወንጀለኞች በቡራዩ፣ከታና አሸዋ ሜዳ በሚኖሩ ሰላማዊ ዜጎች እጅግ አስነዋሪ አረመኔያዊ ጭፍጨፋና ማፈናቀል ተፈፅሟል፡፡ እንዲሁም በጉራጌ ዞን ማረቆና ወለኔ በተከሰተ ግጭት የሰላማዊ ዜጎች ሕይወት ሊቀጠፍ ችሏል፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው የኢፌዴሪና ክልል መንግስታት ህግና ሥርዓትን የማስከበር ግዴታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው እንደሆነ አብን ያምናል፡፡

አብን ያነሳቸውን የአማራ ሕዝብ የኅልውና ጥያቄዎች የእኔም ጥያቄዎች ናቸው፤የአማራ ብሔርተኝነትም ከእንግዲህ መመሪያዬ ነው በማለት በነሐሴ ወር ባወጣው መግለጫ ያስደመጠን ብአዴን አስቀድሞ ያወጣውን የራሱን መግለጫ በማጠፍ ከሰሞኑ ሌላ አስቂኝ መግለጫ አውጥቷል፡፡ የብአዴን የሰሞኑ መግለጫ የአማራ ሕዝብ በብአዴን ላይ የነበረውን የተስፋ ጭላንጭል ጨርሶ ያጠፋ መሆኑን አብን ይገነዘባል፡፡ ለራሱ ውሳኔ ተገዥ ያልሆነ ድርጅት ላይ ተስፋ ማድረግ ጉም የመዝገን ያህል አዳጋች መሆኑንም ተገንዝበንበታል፡፡

በአጠቃላይ ያለፉትን ሦስት ወራት አገራዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ስንገመግማቸው ለአማራ ሕዝብ ቀጣዩ ጊዜ ካለፈው ቢብስ እንጂ የማይሻል መሆኑን ፤ በጣረሞት ላይ ሆኖ ባዶ መደመርና ፍትኅ-አልቦ ይቅርታን የሚያነበንበው የኢህአዴግ አፋኝ ሥርዓት እንደአገር ሁላችንም አሸናፊ የምንሆንበትን ሥርዓት ለመዘርጋት ያቃተው መሆኑን ፤ መንግሥት ህግና ሥርዓትን በአግባቡ ማስከበር ባለመቻሉ በየአካባቢው የደቦ ፍርድና ዘግናኝ ጅምላ ጭፍጨፋዎች መበራከታቸውን አብን ታዝቧል፡፡

ስለሆነም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ – አብን፡-

 1. መንግስት የአማራ ሕዝብ የኅልውና ጥያቄዎችን በአስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጥ እንጠይቃለን፡፡
 2. መንግስት የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት የማስጠበቅ ግዴታውን በአግባቡ እንዲወጣ ይጠይቃል፡፡ ተጎጂዎችንና ተፈናቃዮችን በፍጥነት መልሶ እንዲያቋቁም አብን ይጠይቃል፡፡
 3. መንግስት ከእርቅ በፊት እውነታን የማጣራት ሥራ እንዲሰራ ፤ በዘር ማጥፋት ፣ ጅምላ ጭፍጨፋ ፣ አገር ማፍረስና ከፍተኛ ዘረፋ ወንጀሎች ላይ የተሳተፉ አካላትን ለሕግ እንዲያቀርብ ፤ ለተጎጂዎችም በመንግስት ደረጃ ይቅርታ እንዲጠይቅና የልማት ካሳ እንዲከፍል እንጠይቃለን፡፡
 4. መንግስት የፖለቲካ ኃይሎችንና ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ሁሉንአቀፍ ስልጡን ውይይቶችና ድርድሮች ያለቅድመ-ሁኔታ እንዲካሄዱ በማመቻቸት እንደአገር ሁሉም ኃይሎች አሸናፊ የምንሆንበትን መድረክ እንዲያመቻች እንጠይቃለን፡፡
 5. ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከርዕዮተዓለምና ጎሳ አጥር ወጥተው ህዝቦችን በእኩልነትና ፍትኃዊነት የምታስተናግድ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የመገንባት ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ እንጠይቃለን፡፡
 6. ለአማራ ሕዝብና ለኢትዮጵያ ወዳጅ የሆኑ አገራትና ዓለማቀፍ ተቋማት የአማራ ሕዝብ የኅልውና ጥያቄዎችን ተገንዝበው ከጎናችን እንዲቆሙ ፤ እንዲሁም ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማሸጋገር የሚደረገውን ሁሉንአቀፍ ጥረት እንዲደግፉ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
 7. መላው የአብን አባላትና ደጋፊዎች ለአማራ ሕዝብ የኅልውና ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘትና አገርን ወደ ዴሞክራሲ ሥርዓት የማሸጋገር እልህ አስጨራሽ ትግል ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ ወትሮ ዝግጁነታቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
 8. መላው የአማራ ሕዝብና ኢትዮጵያውያን በሙሉ፡- አብን የያዘው ፕሮግራም የአማራን ህልዉና ከማስከበር ባለፈ ለአገራችን መልካም ዕድል ይዞ የሚመጣ ፣ ሁሉንም በእኩልነትና ፍትኃዊነት ተጠቃሚ የሚያደርግና አገርን ከመፍረስ የሚታደግ መሆኑን ተረድተው ከንቅናቄያችን ጎን ተሰልፈው በጽናት እንዲታገሉ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

በመጨረሻም ከሰሞኑ ጭካኔ በተሞላበት መልኩ ግድያ ለተፈፀመባቸው የመተከልና የአዲስ አበባ ዙሪያ ወገኖች ነፍስ ይማር እያልን ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን እንመኛለን፡፡ የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው ወገኖችም በቶሎ እንዲያገግሙ መልካም ምኞታችንን እናስተላልፋለን፡፡ መንግስት ገለልተኛ አጣሪ ቡድን በማቋቋም በዚህ ወንጀል ድርጊት የተሳተፉ ግለሰቦችንና አካላትን ለፍትኅ እንዲያቀርብም አብን በአፅንዖት ያሳስባል፡፡

ክብርና ሞገስ ጭቆናንና አፈናን በመቃወም ሰማዕትነት ለተቀበሉ ወገኖቻችን!

አማራ በልጆቹ ትግል ህልዉናዉን ያስከብራል !

እናመሰግናለን!

Leave A Reply

Your email address will not be published.