Take a fresh look at your lifestyle.

ቄሮ ማነው? ምንስ ነው ?(በዮናታን ወልዴ)

– “ቄሮ የዚች ሀገር የፌደራሊዝም ዋስትና ነው”

– “ቄሮ የዚህች ሀገር የሰላም ዋስትና ነው”

– “ቄሮ አሁን ያለው የለውጥ ሂደት ደጀን ነው”

እነዚህ መገለጫዎች እራሱን የቄሮ መሪ ነኝ በሚለው ጃዋር መሀመድ ቃል በቃል የተነገሩ ናቸው:: ከዚህም አልፎ ጃዋር “እዚህ ሃገር ውስጥ ሁለት መንግሥት አለ አንዱ አብይ የሚመራው መንግሥት ሲሆን ሌላው የቄሮ መንግስት ነው” ይለናል::

በተጨማሪም ላለፉት 27 ዓመታት የአምባገነን ስርዓት ባለቤት የነበረውን አካል እጅ ጠምዝዞ፣ ከተጋረደበት ሼል ቅርፊቱን ቀርፍፎ መውጣት የቻለው የለውጥ ኃይልም ሳይቀር በየመድረኩ ያንቆለጳጵሰዋል:: የለውጡ ዋንኛ ተዋናይ ነው ይለዋል::

በእርግጥም አሁን ያለው ለውጥ እንዲመጣ ባለፉት ተከታታይ 3 ዓመት ገደማ በሃገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች የህዝብ እምቢተኝነት ያለማቋረጥ ተስተውሏል:: ለዚህም የትግል ሂደት ፈር ቀዳጅና አብዛኛውን ሊባል በሚችል መልኩ ድርሻውን በኦሮምያ ክልል እና አካባቢው ያሉ ወጣቶች ይወስዳሉ:: የዚህም ትግል ውጤት በመንግስት ደረጃ የክልሉ ወኪል ወደሆነው ኦህዴድ ሰርፆ በመግባት ዛሬ ወደ አመራር የመጣውን “ቲም ለማን” ወልዷል ሊባል ይችላል:: ኦህዴድ አለቃው ለነበረው ህወሃት አልታዘዝም ማለት መጀመሩ፣ አድርባይ የነበሩ የድርጅቱ አመራሮችን እየቀረፈ መጣሉ፣ በክልሉ ላይ ባለሙሉ ስልጣን መሆኑን ማረጋገጥ መቻሉ፣ ላለፉት 27 ዓመታት “ጠላትህ ነው” እየተባለ ሲነገረው ከነበረው የአማራ ህዝብ እና በመንግስት የህዝቡ ተወካይ ከሆነው ድርጅት “ብአዴን” ጋር ቅርርብ መፍጠር መቻሉ የቅርብ ግዜ ትዝታዎች ናቸው::

ይህም ሁኔታ የለውጥ ሃይሉን አቅም በማደርጀት አጠቃላይ የኢህአደግን እና የመንግስትን ቅርፅ ለመቀየር አስችሎታል:: በዚህም ምክንያት ሀገሪቱ ከቀደሙት ዓመታት የተሻለ በሚባል መልኩ ወደ መልካም አስተዳደር እና ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው የውጪ ፖሊሲ አቅጣጫ ፊቷን ማዞር ችላለች:: ከነዚህም ውስጥ ህዝቡን ለማፈኛነት ሲውሉ የነበሩ የተለያዩ ህጎችንና የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን ማንሳት፣ ሽብርተኛ ተብለው ከተፈረጁ ድርጅቶች ጋር ስምምነት መፍጠርና ሃገር ውስጥ ገብተው በህጋዊ መንገድ በፖለቲካው ውስጥ እንዲሳተፉ ማድረግ፣ በማንኛውም የፖለቲካ ልዩነት ምክንያት የታሰሩ ሰዎችን መፍታት፣ የግልና የመንግስት ሚድያዎች በነፃነት እንዲሰሩ ክፍት ማድረግ፣ ለዓመታት በጠላትነት ከተፈረጀው የኤርትራ መንግስት ጋር እርቅ በማውረድ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የጠበቀ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መፍጠር ዋንኞቹ ሊባሉ ይችላሉ::

እነዚህ በተግባር የታዩ ለውጦች ሃገሪቷ ፅኑ የሆነ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመትከል የምታደርገውን ጉዞ አመላካች ይመስላሉ::

– ከላይ እንደተገለጸው በየአካባቢው በእምቢ ባይነት የተነሱ ወጣቶች ለዚህ ለውጥ መምጣት ትልቅ ድርሻ አላቸው:: በየክልሉ የተነሱት ወጣቶች እንደየክልላቸው ቄሮ፣ፋኖ፣ዘርማ… የሚሉ ስሞች ለራሳቸው በመስጠት ተደራጅተው ለለውጥ ሲታገሉ ቆይተዋል:: ይህ ለውጥ መታየት ከጀመረ በኃላ ግን ከቄሮ ውጪ ያሉት ቡድኖች ህጋዊ እና ሰላማዊ የሆኑ ድርጅቶችን በመቀላቀል ወይም ወደ ህጋዊ ድርጅትነት ራሳቸውን በመቀየር የቀደመውን የቡድን ቅርፃቸውን እያደበዘዙት እና እያጨለሙት መጥተዋል::

 

ቄሮ ግን አሁንም አወዛጋቢ በሆነ መልኩ እንቅስቃሴውን ቀጥሏል:: የለውጥ መንስዔ መሆኑ የሚነገርለት ብቸኛ መልካም ጎኑ ሲሆን ከለውጡ ዋዜማ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ለብዙ ሰዎች ህይወት ህልፈት፣ የንብረት ውድመት እና ከቅርብ ግዜ ወዲህ ደግሞ የዘር ግጭትና ጭፍጨፋ ላይ በተደጋጋሚ ስሙ እየተነሳ ነው:: አሁን ያለው መንግስት በውጪ ሃገር የነበሩ የሽምቅ ተዋጊ ቡድኖችን ትጥቅ ፈተው ወደ ሃገር ውስጥ ገብተው በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ በፖለቲካው መድረክ እንዲወዳደሩ ሲያመቻች ሃገር ውስጥ ያሉትን “ኃይሎች” ወደ አንድ ወይም ተመሳሳይ አቅጣጫ ማምጣት ለምን አልቻለም?

– ይህ አካል/ኃይል እውነትስ ማነው?

– አላማው እና ግቡስ ምንድነው?

– ከዚህ በኃላ ላለው የዲሞክራሲ ጉዞስ አስተዋፅኦው ምን ሊሆን ይችላል?

– የሲቪክ ማህበር ነው?

– የፖለቲካ ፓርቲ ነው?

– ህጋዊ ማንነት አለው?

– እውነትስ እንደተባለው በሃገሪቷ ውስጥ ሁለተኛ መንግስት ሆኗል?

ተጨማሪ ጥፋቶች፣ አላስፈላጊ የዘር ግጭቶች አልፎ ተርፎም ሃገሪቷ ወደማያባራ ውጥንቅጥ ውስጥ ከመግባቷ በፊት መንግስት እና የሚመለከታቸው አካላት እነዚህ ጥያቄዎች በአስቸኳይ መልስ እንዲያገኙ ማድረግ ይኖርበታል::

Leave A Reply

Your email address will not be published.